ቅዱስ ሙሴ ጸሊም ክፍል 1 / Saint Moses the Black Part - 1

የቅዱሳን ታሪክ / Yekidusan Tarik
የቅዱሳን ታሪክ / Yekidusan Tarik
237.9 هزار بار بازدید - 6 سال پیش - በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን
​​ታላቁ አባት አቡነ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ተጋድሎአቸውን የፈጸሙት ግን በግብፅ ነው፡፡
መጀመሪያ ላይ እንደ አብርሃም በየዋህ ልቡና ሆነው ስነ ፍጥረትን በመመራመር
እግዚአብሔር አምላካቸውን ያገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወላጆቻቸው ፀሐይ
ያመልኩ ስለነበር ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ‹‹ተው አምላካችን
ፀሐይ ይጣላሃል›› ይሏቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ባደጉ ጊዜ ቀማኛ ዘራፊ ሆኑ፡፡
እየዘረፉ ብዙ ይመገቡ ስለነበር ከትልቅነታቸውና ኃይለኛነታቸው የተነሳ ‹‹በገ
ፈጅ›› እየተባሉም ይጠሩ ነበር፡፡
ብዙ ወርቅ ከባለ ሀብቶች ሰብስባ ለነዳያንና ለቤተክርስቲያን ልትሰጥ ትሄድ
የነበረችን አንዲት ክርስቲስቲያን ሴት ልጅ ሙሴና ግብረ አበሮቻቸው ለወርቁ
ሲሉ እርሷንም ማርከው ወሰዷት፡፡ ማታ ላይ ስለ ውበቷ ሲያወሩ እርሷ ግን
‹‹ስምህ ማን ነው?›› ስትላቸው ‹‹ሙሴ ነኝ›› ቢሏት ‹‹ይሄ ስምኮ እጅግ የተባረከ
ስም ነው….›› ብላ ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴና ስለ ክርስቶስ አስረዳቻቸው፡፡ ከዚህ
በኋላ በወላጆቻቸው ስለ ፀሐይ አምላክነት ሲነገራቸው ያደጉትን ነገር
መመርመር ጀመሩ፡፡ ‹‹ፀሐይ አምላክ ከሆነ እስከዛሬ ድረስ ሽፍታና ዘራፊ ሆኜ
ሰው ስገድልና ይህን ሁሉ ኃጢአት ስሠራ እንዴት ፀሐይ ሳታቃጥለኝ ቀረች?
ደግሞም ፀሐይ ጠዋት ወጥታ ማታ ትጠልቃለች ይህችስ እንዴት አስገኚ
ልትሆን ትችላለች ለራሷ አስገኚ አላት እንጂ…›› በማለት ፀሐይን፣ ጨረቃን፣
እሳትን፣ ነፋስን በየተራ አምላክ መሆናቸውን አለመሆናቸውን በሚገባ ከፈተኑና
ከመረመሩ በኋላ ‹‹የፀሐይ የጨረቃ የሁሉ አስገኚ አምላክ ተናገረኝ›› ብለው
ሲጸልዩ ከሰማይ ድምፅ መጥቶላቸው ወደ ገዳም ሄደው ከአባቶች ትምህርተ
ሃይማኖትን እንዲማሩ ተነገራቸውና ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደው መምህር
ኤስድሮስ ሁሉንም ነገር አስተምረው ለማዕረገ ምንኩስና አበቋቸው፡፡
መጀመሪያ ወደ ገዳሙ ሲሄዱም ይዘርፉበትና ይቀሙበት የነበረውን ስለታም
መሣርያ እንደያዙ ስለነበር ያዩአቸው መነኮሳት ሁሉ ‹‹ሊገድለን መጣ›› ነበር
ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ለመነኮሳቱ ሁሉ የሚላላኩ ሆኑ፡፡ ትንሹም ትልቁም ‹‹ሙሴ
ይህን አድርግልኝ›› ይሉታል እርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፡፡ ራሱን በትሕትና ዝቅ
በማድረግ በተጋድሎ እየኖረ ተአምራትን ማድረግ ጀመረ፡፡ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንብ
ነበር፤ ለቅድስና ደረጃ ከበቁም በኋላ 40 ዓመት ሙሉ ከሰው ሳይገናኙ ብቻቸውን
ዘግተው ከኖሩ በኋላ ለ500 መነኮሳት አበምኔት ሆነው ተሾሙ፡፡ ቀን ወንጌል
ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት እየተነሱ ከበረሃ ሄደው ለሁሉም መነኮሳት ውኃ
ይቀዱላቸው ነበር፡፡ አገልግሎታቸው የታይታ እንዳይሆንባቸው አረጋውያን
መነኮሳት መተኛታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የግብፅ በረሃን አቋርጠው ከሩቅ ሥፍራ
ሄደው ውኃ እየቀዱ መነኮሳቱ ሳያዩአቸው በየደጃፋቸው ላይ ያስቀምጡላቸው
ነበር፡፡
ብዙ መነኮሳትም ወደ አቡነ ሙሴ እየመጡ የሕይወትን ትምህርት ይማሩ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት
የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባ
ሙሴም ‹‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት››
አሉት፡፡ ‹‹ሌላ አይጠበቅበትምን?›› ሲል ያ ወንድም ጠየቃቸው፡፡
‹‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ኃላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው
ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልንጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ
ጌታችን የግብፅን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት
አልነበረም›› ብለው መለሱለት፡፡ ያም ወንድም ‹‹ምን ማለት ነው?›› አላቸው፡፡
እሳቸውም ‹‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል
አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡
ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት
ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣
ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ
አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ
መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ሁሉንም
እግዚአብሔር ያውቃል በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም
አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ
ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሀሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን
እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም
ማግኘት ማለት ይህ ነው…›› ብለው መከሩት፡፡
በዕድሜአቸው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ለመቀበል ከመነኮሳት ደቀ
መዛሙርቶቻቸው ጋር ወደ አባ መቃርስ ሄዱ፡፡ አባ መቃርስም ‹‹ልጆቼ ከናንተ
መካከል በሰማዕትነት የሚሞት›› አለ ብለው ትንቢት ሲናገሩ ሙሴ ጸሊምም
‹‹አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ፣ ‹ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ› የሚል ቃል አለ፡፡
ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር›› አላቸው፡፡ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች
ገዳሙን ዘርፈው መነኮሳቱን ሊገድሉ ሲመጡ ደቀመዛሙርቶቻቸው ‹‹ሸሽተን
እናምልጥ›› ሲሏቸው አቡነ ሙሴ ግን ‹‹በጎልማሳነቴ ጊዜ ደም አፍስሼያለሁና
አሁን የእኔም ደም ሊፈስ ይገባል›› በማለት ራሳቸውን ለመሰየፍ አዘጋጅተው
ጠበቋቸውና በርበሮች ሰኔ 24 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ ቆርጠዋቸዋል፡፡
ፈርተውና ሸሽተው የነበሩት ደቀመዛሙርቶቻቸውም ተመልሰው አብረዋቸው
ተሰይፈዋል፡፡
የአባታችን የሙሴ ጸሊም ቅዱስ ሥጋቸው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፡፡
ግብፆች አቡነ ሙሴ ጸሊምን በእጅጉ ያከብሯቸዋል፡፡ በስማቸው ጽላት ቀርጸው
ቤተክርስቲያን ሠርተው ሥዕላቸውን አሠርተው ገድላቸውን ጽፈው
በስንክሳራቸው መዝግበው የዕረፍታቸውን መታሰቢያ በደማቅ ሁኔታ ነው
የሚያከብሩት፡፡ የአቡነ ሙሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው
ይማረን፡፡ ኣሜን
6 سال پیش در تاریخ 1397/10/12 منتشر شده است.
237,976 بـار بازدید شده
... بیشتر